አልአሙዲ ለኢህአዴግ ሲቀሰቅሱ ዋሉ

ሼህ ሙሀሙድ ሁሴን አልአሙዲ የኢህአዴግ አርማ የሆነውን የንብ ምልክት ያለበትን ቲሸርት ለብሰው ቁጥሩ ከ5 ሺህ ለማያንስ ህዝብ ቅስቀሳ ማካሄዳቸው ታወቀ። የቅዱስ ጊዮርጊስ አርማ የሆነውን የእንግሊዝኛ የV ምልክት ወይም ቅንጅት አሁን እየተጠቀመበት ያለውን ምልክት መውሰዱን እንደሚቃወሙም ገልፀዋል።

ሼህ አላሙዲ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 15 ቀን 1997 ዓ.ም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር አዲስ ስታዲየም ለማስገንባት በሲ.ኤም.ሲ አካባቢ በተገኙበት ዕለት የኢህአዴግ አርማ የሆነውን የንብ ምልክት ያለበትን ቲሸርት ለብሰው በመምጣታቸው ብዙዎችን አስገርመዋል አስቆጥተዋልም። አንዳንድ ሰዎች እንደተናገሩት አጋጣሚውን ምክንያት በማድረግ ሺህ አላሙዲም ሆኑ አቶ አርከበ ህዝቡ ንብን እንዲመርጥ መቀስቀሳቸው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ቡድንና ለስፖርት እድገት በአጠቃላይ አደገኛ ነው። በተለይ ሼህ አላሙዲን የቅንጅትን ስም ሳይጠቅሱ «አርማችንን ተቀምተናል ቢሆንም እናስመልሳለን» ማለታቸው በወቅቱ በሥፍራው የነበሩትን የቅንጅት ደጋፊዎች እጅግ አበሳጭቷል።

ስታዲየሙን ለማስገንባት ከሚፈጀው 50 ሚሊዮን ብር ውስጥ ሼህ አላሙዲ 40 ሚሊዮን የሚሸፍኑ ሲሆን ቀሪውን 10 ሚሊዮን ደግሞ ህብረተሰቡ እንደሚሸፍን ተገልጿል። በስነ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ሀይሌ ገብረ ስላሴን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተዋል። ከአርቲስቶችም ጥላሁን ገሰሰ፣ ሙሀሙድ አህመድ፣ ሚኒሊክ ወስናቸውና ሌሎችም የተገኙ ሲሆን ጥላሁን ገሰሰም በስፍራው ለተገኘው ህዝብ ዜማውን አሰምቷል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ጥቅምት 19 ቀን 1990 ዓ.ም በቀራንዮ አካባቢ በተሰጠው መሬት ላይ ስታዲየም ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጡ የሚታወስ ሲሆን ስታዲየሙ ግን ሳይገነባ መቅረቱ ይታወቃል።

የስታዲየሙን የመሠረት ድንጋይ አቶ አርከበ እቁባይ የአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ያኖሩ ሲሆን ግንባታውም በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል።

በሼህ ሙሀመድ አላሙዲ ድርጊት ላይ አስተያየት የሰጡን አንድ ግለሰብ «ምንም እንኳን ግለሰቡ ኢትዮጵያን የሚወዱና በብዙ ኢትዮጵያውያንም ዘንድ የሚወደዱ ቢሆንም ይህ አድራጎታቸው ከኢህአዴግ ጋር የተለየ ግንኙነት ይኖራቸው ይሆናል የሚል ጥርጣሬን እንደሚፈጥርና በህዝብ ያላቸውን ተወዳጅነትም እንዳይቀንስባቸው ያሰጋል» ብለዋል። በተለይ እሳቸው በህግ የኢትዮጵያ ዜጋ ባለመሆናቸው እና የውጭ ዜጋ በመሆናቸው እንዲህ አይነቱን ድርጊት መፈፀም አልነበረባቸውም ብለዋል።

ከአዲስ ዜና ሚያዝያ 18 ቀን 1997

ሰለ እዚህ ዜና ዋርካ ስር በአማርኛ ይወያዩ !