የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፓርላማ አባላት በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ውስጥ አባሎቻቸው እንዲወከሉ ጠየቁ። የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሽፈራው ጃርሶ ይህ ሊሆን የሚችለው ታማኝ ተቃዋሚ ሲኖር ነው ብለዋል።
በምክር ቤቱ የትላንት ውሎ ላይ አፈ ጉባዔው በተጠቀሰው አጀንጃ ላይ ም/ቤቱን እንዲወክሉ ሦስት የኢሕአዴግ ተመራጭ አባላትን የሰየሙ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢያንስ ውክልና አይኖረንም ሲሉ ተቃውመዋል።
የኦፌዴን ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የአገሪቱን የሕግ ሥርዓት ማስተካከል የሚቻለው በአንድ ፓርቲ ተሳትፎ ብቻ አይደለም። ኢሕአዴግ ቢያንስ በዚህ እንኳን ተቃዋሚዎችን ሊያሳትፍ ይገባል። ይህ መሆኑም የአገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት ይጠቅማል ብለዋል።
ኢሕአዴግ የሚወደውን አባሉን አንስቶ በዚህ ጉባዔ ውስጥ በማስቀመጡ ብቻ የአገሪቱ የሕግ ሥርዓት በአግባቡ እየሰራ አይደለም። ኢሕአዴግ አሁንም የሕዝቡን አመኔታ ለማግኘት በአንድ መንገድ ብቻ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም ይህ እርምጃ የፍትሕ ሥርዓቱን በአንድ ፓርቲ ሥር እንዲወድቅ ለማድረግ እና የፍትሕ ሥርዓቱን መሪ በተፈለገበት አቅጣጫ ለመጠምዘዝ የተደረገ ነው ብለዋል።
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሽፈራው ጃርሶ በተሰነዘሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ተቃውሞ ላይ በሰጡት ምላሽ በእንደዚህ ዓይነት ጉባዔ ውስጥ ተቃዋሚዎች ሊሳተፉ የሚችሉት ታማኝ ሲሆኑ ነው ብለዋል።
ተቃዋሚዎቹ የፓርላማ አባላት ታማኝ ማለት ምን ማለት ነው? በሚል በተደጋጋሚ የጠየቁ ሲሆን ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ጃርሶ ታማኝ ያልኩት ለኢሕአዴግ ሳይሆን ለህግ መንግስቱ ነው ብለዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አፈ ጉባኤው ይህንን አጀንዳ እንዳይፀድቅ እንዲያደርጉ በጥብቅ ቢጠይቁም አፈ ጉባዔው በበቂ ሁኔታ ውይይት የተደረገበት መሆኑን በመግለፅ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።