በአዲስ አበባ ስታዲየም በተፈጠረው ብጥብጥ ምክንያት በርካታ ተመልካቾች ከስታዲየሙ እንደሚርቁ አስታወቁ። የቅ/ጊዮርጊስና የወንጂ ስኳርየእግር ኳስ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ ላይ ብጥብጥ እንዲፈጠር ያደረጉ አካላት ተልዕኮ እንዳላቸው ተጠቆመ። ፌዴሬሽኑ ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ብቃት እንዳለው ገልጿል። የቅ/ጊዮርጊስና የወንጂ ስኳር ቡድኖች ተበደልን እያሉ ነው።
አሳፋሪ የተባለው የአዲስ አበባ ስታዲየም ረብሻ የተከናወነው መጋቢት 15 ቀን 1997 ዓ.ም ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነበር። ረብሻው ከተጨዋቾች አልፎ ደጋፊ አጥር ጥሶ የገባበት በመሆኑ ከፖሊስ ቁጥጥር ውጭ ሊሆን ችሏል። ኳስ ለመመልከት በክብር ትሪቡን በኩል የተቀመጡ ተመልካቾች እንደገለጹት «በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲህ ያለ ስርዓት የለቀቀ ረብሻ ተፈጥሮ አያውቅም»
ጨዋታው ሁለት ለሁለት በሆነ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ አስራ ሶስት ቁጥር ለብሶ ሲጫወት የነበረው የወንጂው ፍቅረአብ ቡባም የቅ/ጊዮርጊሱን አብርሃም ቺባን በቦክስ መማታቱ ምክንያት የተቀሰቀሰው ረብሻ በገላጋይ ስም የሁለቱም ቡድኖች ተጨዋቾች ቡጢ የተለዋወጡበት ነበር። የወንጂ እግር ኳስ ቡድን የቡድን መሪ አቶ አለማየሁ ከበደ «ተጨዋቾቻችን በሙሉ ተደብድበዋል። ጥርሱ የተነቃነቀ፣ የተቀጠቀጠና በዓይኑ ላይ ጉዳት የደረሰበት ተጨዋች አለ»በማለት ከአሁን በኋላ አዲስ አበባ ስታዲየም ገብቶ ለመጫወት ፍርሃት እንዳደረባቸው ገልፀዋል። ፀቡን የፈጠረው የወንጂ ተጨዋች ነው ለተባለው «አይቻለሁ፣ ተጨዋቾቹንም ጠይቄያለሁ በክብር አይኑ ላይ ተመቶ የተጎዳ ተጨዋጭ የመማታት አቅም የለውም» በማለት ረብሻውን የፈጠሩት የቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋቾችና ደጋፊዎች መሆናቸውንና የእለቱ ዳኛ ለጥፋቱ መባባስ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ጠቁመዋል።
የቅ/ጊዮርጊስ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ በበኩሉ «ለመገላገል ገብተን በቆመጥ ተደብድበናል»በማለት የነበረውን የፖሊስ ኃይል ወቅሷል። አያይዞም «የእለቱ ዳኛ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምት ከልክለውናል። ይህ የሚያሳየው ፌዴሬሽኑ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የተበላሸ አሰራር መከተሉን ነው» በማለት ተናግረዋል።
«ዳኛ የደበደበ የማይቀጣበት ጥፋት የስራ ዝም የሚባልበት ተቆጣጣሪ ያጣ ፌዴሬሽን ባለበት ሁኔታ ወደፊት የበለጠ ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል ቢያደርጉ መልካም ነው። ይህ ካልሆነ ውድድር የሚደረግበት ሁኔታም አሳሳቢ እየሆነ ነው የሚመጣው» ያለው ደሳለኝ አንድ ተጨዋች የጫረው እሳት የተባባሰው ከፌዴሬሽኑ ደካማነት የተነሳ በቂ ጥበቃ ባለመደረጉ እንደሆነ አመልክቷል።
ፌዴሬሽኑ ውድድር ያዘጋጃል። ዳኛ ይመድባል እንጂ የክለብ ደጋፊዎችን እግር በእግር ሊቆጣጠር አይችልም የሚለው ፌዴሬሽኑ «የተፈጠረውን ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር በተመለከተ በአረንጓዴው መፅሀፍ መሰረት ርምጃ ይወስዳል» ብሏል።
«የተፈጠረው አሳፋሪ ስራ አሳዝኖናል። ሁሉም ነገር የሚዳኘው በሕጉ ነው» ያሉት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው እሸቱ «ፌዴሬሽኑ ህጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ሁሉም ዓይነት ብቃት አለው» ብለዋል። የፌዴረሽኑ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ «አደጋ እንዳይፈጠር በማተኮር እንሰራለን» አሁን ለተፈጠረው ጉዳት ችግሩ ዳኛው ጋር ከሆነ በዳኞች ኮሚቴ፣ የስነስርዓት ጉዳይ ደግሞ በውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ይታያል። ኮሚቴው የሚያቀርበው የውሳኔ ሃሳብ ለማንም ሳይዳላ ተግባራዊ ይሆናል» ብለዋል።
የዕለቱ የፖሊስ ኃይል አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር ኃይሉ ሃለፎም በበኩላቸው «እግር ኳስ ስሜት ውስጥ የሚከሰት ስፖርት ቢሆንም አውቀው ረብሻ የሚፈጥሩ አጋጥመውናል» ብለዋል። አያይዘውም «እንደ ስፖርት ቤተሰብ ሳይሆን የተለየ ብቀላ የሚፈልጉ አለ» ሲሉ የድርጊቱን አፀያፊነት አመልክተዋል። ሁሉም ነገር ለፖሊስ መተው የለበትም። ፖሊስ ከስፖርት ቤተሰቡ የተለየ ስራ ሊሰራ አይችልም።የትኛውም ቦታ ይህን ፖሊሲ መለዮውን አጥልቆ ከቆመ ህገወጥ የሚሰሩትን አጋልጦ ለፖሊስ መስጠት ከስፖርት ቤተሰቡ ይጠበቃል ያሉት ዋና ኢንስፔክተር «በቀጣይ ያሉት ጨዋታዎች ለሻሚፒዮና፣ ላለመወረድና ነጥብ ላለመጣል ፉክክር ስላላባቸው ጥበቃው ሊጠናከር ይገባል» ብለዋል።